top of page

የልደታን ትምህርት እነሆ!


በዚህ ዕለት የቅድስት ድንግል ማርያምን ዕለተ ልደት “ልደታ ለማርያም” ብለን እናከብራለን ። በቤተ ክርስትያናችን አስተምህሮ መሠረት የነገረ ማርያም ትምህርታችን ግንቦት አንድ ቀን ድንግል መወለዷን ያበሥራል ። በመሆኑም ግንቦት አንድ ቀን በየዓመቱ የልደቷን መታሰቢያ በዓል (በዓለ ልደቷን) ልጆችዋ እናከብራለን።

ቅዱሳት መጻሕፍት እንደ መሰከሩልን እመቤታችን ድንግል ማርያም እግዚአብሔርን ከሚፈሩ ከሐናና ከኢያቄም በጾም በጸሎት በስግደት በስእለት ወደ እግዚአብሔር ሲማፀኑ ከኖሩ በኋላ የለመኑትን የማይነሳ አምላክ


ጸሎታቸውን ድንግል ማርያመን በመስጠት መለሰላቸው ። ድንግል ማርያም ለሐናና ለኢያቄም የጸሎት መልስ ልትሆን የተሰጠች ብቻ ሳትሆን ለሰው ልጆች ሁሉ ማለትም ለአበው ፥ ለነቢያት ፥ ለነገሥታት ፥ ለመሳፍንት ፥ ለካህናት ፥ ለቅዱሳን ሁሉ የጸሎት መልስ በመሆኗ ለመካኗ ዓለም የተሰጠች የሕይወት ስጦታ ናት ።

ሁለቱ ቅዱሳን ወላጆችዋ አምላክ ጸሎታቸውን ከሰማ በኋላ በብሥራተ መልአክ በፈቃደ አምላክ ነሐሴ ሰባት ቀን ተፀንሳ ግንቦት አንድ ቀን እመቤታችን ተወለደች ።

በተፀነሰች ጊዜ ተአምራት እንደ ተደረገ በነገረ ማሪያም ተጽፎአል ። ሐናና ኢያቄምንም በተደረገው ተአምራት ምክንያት አይሁድ ቀንተው በማሳደዳቸው ምክንያት እመቤታችን በሊባኖስ ተራራ ስትወለድ ። አባትዋ ሰሎሞን “ሙሽራዬ ሆይ ፤ ከሊባኖስ ተራራ ከእኔ ጋር ነይ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነይ” ብሎ የተናገረው ተፈጽሞአል ። መኃ ፬ ፥ ፰ ።


ይህ ዕለት ልዑል አምላክ ትሁት ሥጋን ለመንሣት ትሁት ሥጋም በልዑል አምላክ ለመክበር ፣ ሰውና መላእክት አንድ ሁነው ለማመስገን የበቁበትን ምሥጢር ያዘለው የሎዛ መሰላል ሰዋሰወ የዕቆብ የታየበትን ዕለት ይመስለዋል ።

ይህ ዕለት የሲና ሐመልማል የበቀለችበት ዕለት ነው ። ይህ ዕለት የቃል ማደሪያ ታቦተ ሙሴ ፣ ቃሉ የሰፈረበት ጽላተ ሙሴ ፣ ከእግዚአብሔር ለዓለማችን የተሰጠበትን ዕለት ይመስላል ። የአካላዊ ቃል ማደሪያ እመቤታችን ድንግል ማርያም ተወልዳበታለችና ።

ይህ ዕለት የአሮን በትር በወንድማማቾች መካከል በተፈጠረው ጠብ በልምላሜ ምልክትነት ለማጥፋት ለምልማ የተገኘችበትን ዕለት ይመስላል ። የጠብ ማለፊያ የሰላም ማደሪያ የእርቅ እናት ዛሬ ተወልዳለችና ።ይህ ዕለት የጌዴዎን ፀምር የተሠራችበትን ፣ ደመና ኤልያስ የተጋረደችበትን ፣ የኤልያስ መሶብ ተወጥና የተፈጸመችበትን ፣


የኤልሳዕ ማሰሮ መራራውን ለመለወጥ በምንጩ ላይ ከጣፋጭ ጨው ጋር የተቀመጠችበትን ዕለት ይመስላል ።

አምላክ የሚያድርባት መቅደስ የተገለጠችበት ፣ የጽድቅ አባት የሚያርፍባት አዳረሽ ፣ ጽርሕ ንጽሕት የተገኘችበት ፣ የሕይወት እንጀራ የክርስቶስ ማደሪያ መሶበ ወርቅ ድንግል ማርያም በዓለም ፊት አጊጣ የርኁባንን (ለተራቡት) ምግብ ይዛ ለመታየት አካል ዘየአክልን (ለክርስቶስ ማደሪያ የተዘጋጀ አካል) ይዛ ተፈጥራ የታየችበት ቅዱስ ዕለት ነው ። ስለዚህ ሁላችንም በሔዋን ስህተት እንደሞትን የክፉውም ሐሳብ በሔዋን በኩል መጥቶ እንዳንጠፋን ፥ አሁን ደግሞ የመዳናችን ዘመን ሲደርስ “ኆኅትሰ ድንግል ይእቲ እንተ ወለደት ለነ መድኅነ” የተባለች የመድኅን እናት የምሥራቅ በር ድንግል ተወለደችልን ። ከእርሷ ሰው የሆነው መሲሕም ታሪካችንን ለወጠልን ።

ወገኖች ሆይ ! አምላክ የሰውን ልጅ ወዶ ይህን ታላቅ ነገር ለኛ አድርጎልናል ። በእኛም ሊያድር ወዶ መቅደሱን ራሱ አንጿልና በእሱ ደስ ይበለን ። ለአባቶቻችን ሰው ሁኖ እንደሚያድናቸው ፣ የዓለምን የእርግማንና የእንጉርጉሮ ታሪክ የሚለውጥ ቡሩክ ዘር ከአብራካቸው እንዳለ ፣ በዘራቸውም ዓለም እንደሚባረክ ቃል የገባው ጌታ ነፍስና ሥጋን የሚነሣበት ቡሩክ አካል ዛሬ ለዓለም ተሰጠ ። ስጦታውም የተገኘው ከተባረከ ጋብቻ ነበር ። አባታችን አባ ሕርያቆስ “ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተፀነስኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ እም ሐና ወኢያቄም ተወለድኪ” = “ድንግል ሆይ! በኃጢአት ፍትወት የተፀነሽ አይደለም ፥ በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ» እንዳለ ።

ይህ ዕለት መርገም በሰፈነበት ፥ እሾህ በሚበቅልበት ምድር ፈንታ አዲስ ምድር ያለዘር የሚያበቅል ምድር-ቅድስት ፣ ጽድቅ ሊሰፍንባት ምድር ቅድስት የተገለጠችበት ዕለት ነው፤ በምድረ ፋይድ ለእኛ ምድር-ቅድስት ሁና የታየችበት ዕለት ነው ። ይህችም ምድር ዕፀ ሕወትን ያፈራች ሐረግ ፣ ሐረገ ወይን ክርስቶስ የበቀለባት አዲስ ምድር ቅድስት ድንግል ማርያም ናት ።

ይህ ዕለት የኖህ ቀስተ ደመና የታየችበት ዕለት ትመስላለች፤ ማየ አይኅን (የጥፋት ውኃን) ባዘነበችው ሰማይ ፈንታ ዳግሚት ሰማይ (ሁለተኛ ሰማይ) ቅድስት ድንግል ማርያም የጽድቅ ፀሐይ መውጫ ፣ የንጋት ኮከብ መፍለቂያ ፣ ዝናመ ምሕረትን ልታወርድልን በደመና ሣህል ተከባ የታየችበት ዕለት ነውና።

ይህ ዕለት የጠላት ምክር በሰማችው ሔዋን ፈንታ የሕያዋን እናት ቅድስት ዳግሚት ሔዋን የወደቀው መልአክ የማየደፍራት ፣ የብርሃን መልአክ በከበረ ሰላምታ ተፈሥሒ ! ተፈሥሒ ! የሚላት ድንግል ማርያም የተወለደችበት ዕለት ነው ።

ይህ ዕለት በኖኅ ልጆች በሐናና በኢያቄም ይዘጋጅ የነበረው የዕረፍት መርከብ ተሠርቶ ያለቀበት ፣ ፍጥረት ከጥፋት የተሠወረበት ፤ ሰው ሁሉ የተረጋጋበት ፤ የዕረፈት እናት ፣ የመሲሑ ማደሪያ ሐመረ ኖኅ እመቤታችን የተወለደችበት ዕለት ነው።

ይህ ዕለት የጥፋትን ውኃ መጉደል ለማብሠር የመስቀሉን የምሥራች ይዛ ወደ ዓለማችን የዋሂት ርግብ ድንግል ማርያም የተላከችበት ዕለት ነው ።

ሥነ ጥቅስ ዘየኀብር በምሥጢር

1/ “አዳም ወሠናይት ጽዕዱት ውብርህት እኅቶሙ ለመላእክት ማርያምሰ ተኀቱ ውስተ ከርሱ ለአዳም ከመ ባሕርይ ጸዐዳ እንተ ሠረፀት አም ሥርወ እሴይ ወተወልደት እም ዘርዐ ዳዊት በምደረ ይሁዳ”

በአማርኛ ፥ “መልካም ውብ የምታበራና የምታንፀባርቅ የመላእክት እኅታቸው ማርያምስ እንደ ነጭ ዕንቈ በአዳም ባሕርይ ታበራለች ፣ ከእሴይ ዘር የተገኘች የበቀለች ፥ (የለመለመች) ከዳዊት ዘር በምድረ ይሁዳ ተወለደች” (መኀትው ዘቅዱስ ያሬድ) ።

2/ «ቆምኪ ርእዮትኪ ወክሳድኪ ከመ አርማቆስ እኅትነ ይብልዋ መላእክት በሰማያት ስብሕት በሐዋርያት ኢያቄም ወለዳ ደብተራ ዘትዕይንት ጥዕምት በቃላ ወሠናይት በምግባራ እግዝትነ ማርያም» ።

በአማርኛ ፥ «ቁመትሽ ፥ መልክሽ ፥ አንገትሽም እንደ አርማስቆስ ነው ። መላእክት በሰማያት እኅታችን ይሏታል ። በሐዋርያት የተመሰገነች ናት ። ኢያቄም ወለዳት (ከኢያቄም ተወለደች) የእስራኤል ሕዝብ (የእግዚአብሔር ጉባኤ) መጠለያ ድንኳን ናት ። አነጋገሩዋ የሚጣፍጥ ፥ በሥራዋ ያማረች ናት» (ዋዜማ ዘቅዱስ ያሬድ) ።

3/ “ምሥራቀ ምሥራቃት ሙጻዐ ፀሐይ ፥ እግዝትየ ዘመና ሙዳይ፥ ተወለደት ዮም ዳግሚት ሰማይ”።

በአማርኛ ፥ “ከምሥራቆች የከበርሽ ምሥራቅ የጽድቅ ፀሐይ የኢየሱስ መውጫ (እናት) የመና መሶብ እመቤቴ ሁለተኛዋ ሰማይ ዛሬ ተወለደች” (የነግሥ ዚቅ)።

4/ “ኦ ድንግል አኮ በፍቶተ ደነስ ዘተፀነስኪ ኣላ በሩካቤ ዘበህግ እምሐና ወኢያቄም ተወለዲኪ”።

በአማርኛ፥ “ድንግል ሆይ፥ በልተው ጠጥተው በሚያደርጉት የሥጋ ፍትወት የተጸነስሽ አደለሺም። በሕገ ከሆነ ሩካቤ ከሀናና ከኢያቄም ተወለድሺ እንጅ።”(ቅዳሴ ማርያም)።

“በእንተ ሐና እምኪ ወኢያቄም አቡኪ ማኅበረ ዮም ድንግል ባርኪ”።

በአማርኛ፥ “ስለ እናትሽ ስለ ሐና ስለ አባትሽ ስለ ለኢያቄም ብለሽ ድንግል ማኅበራችንን ባርኪልን” (ጸሎት ዘዘወትር) … አሜን።

«ለዘላለም ማረፊያዬ ናት» (መዝ131፥14)።

«ተወልደት ዮም ዳግሚት ሰማይ=ሁለተኛዋ ሰማይ ዛሬ ተወለደች »


መምህር ኤፍሬም አሰፋ
144 views0 comments

Commentaires


bottom of page