ቅዱስ ሚካኤል
ቅዱስ ማለት ልዩ፥ ክቡር ማለት ነው፤ ሚካኤል ማለት ደግሞ «መኑ ከመ
አምላክ፥ እንደ እግዚአብሔር ያለ ማነው?» ማለት ነው። ሚካኤል
የሚለው ስም ቃሉ የዕብራይስጥ ነው፤ ሚ - የሚለው «መኑ» ማለት
ነው፥ ካ - የሚለው «ከመ» ማለት ሲሆን፥ ኤል - ማለት ደግሞ
«አምላክ» ማለት ነው።
ይህን ማለትም የቅዱስ ሚካኤልን ስም በጠራን ቊጥር የምንመሰክረው
ስለ እግዚአብሔር ነው፤ በመሆኑም እግዚአብሔርን በባሕርይ
የሚመስለው፥ በሥልጣንም የሚተካከለው፥ በምድርም በሰማይም
እንደሌለ የሚናገር ልዩ፥ ክቡር ስም ነው። የነቢያት አለቃ ሙሴ ባሕረ
ኤርትራን ለሁለት ከፍሎ ሕዝቡን ያሻገረለትንና ፈርዖንን ከነሠራዊቱ
ያሰጠመለትን አምላክ እግዚአብሔርን በመዝሙር ሲያመሰግን፥ «አቤቱ
በአማልክት መካከል (በስም አማልክት ከሚባሉ፥ በስመ አማልክት
ከሚጠሩ፥ አንድም አማልክት ዘበጸጋ ከተባሉ ከነቢያት ከካህናት መካከል)
አንተን የሚመስል ማነው? በቅዱሳንም ዘንድ እንደ አንተ የከበረ ማነው?»
ብሏል። ዘጸ ፲፭፥፲፩።
ቅዱስ ዳዊትም፦ «አቤቱ፥ ከአማልክት የሚመስልህ የለም፤» ብሏል።
መዝ ፹፭፥፰።
፩፥፩፦ «ስሜ ድንቅ ነውና ለምን ትጠይቃለህ?» መሳ ፲፫፥፲፯ የእስራኤል
ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ በመሥራታቸው፥ እግዚአብሔር
በፍልስጥኤማውያን እጅ ለአርባ ዓመት አሳልፎ ሰጥቷቸው ነበር.። በዚህ
ዘመን ከዳን ወገን ማኑሄ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፥ ሚስቱም መካን
ስለነበረች ልጅ አልወለደችም ነበር።
የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ እንደምትፀንስ፥ ወንድ ልጅም
እንደምትወልድ፥ ልጁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ለእግዚአብሔር የተለየ
ናዝራዊ እንደሚሆን ነገራት። የሚያሰክር መጠጥ እንዳትጠጣ፥ የረከሰም
ነገር እንዳትበላ፥ በልጁም ራስ ላይ ምላጭ እንዳይደርስ (ፀጉሩን
እንዳትላጨው) አስጠነቀቃት። እርሷም ተመልሳ የሆነውን ሁሉ ለባሏ
ነገረችው፤ «የእግዚአብሔር ሰው ወደ እኔ መጣ፥ መልኩም እንደ
እግዚአብሔር መልአክ እጅግ የሚያስደነግጥ ነበረ፤ ከወዴትም እንደመጣ
ጠየቅሁት፥ እርሱም ስሙን አልነገረኝም፤» አለችው።
ማኑሄም፥ «ጌታ ሆይ፥ ወደ እኛ የላክኸው የእግዚአብሔር ሰው እባክህ
እንደገና ወደ እኛ ይምጣ፤ ለሚወለደውም ልጅ ምን እንደምናደርግ
ያስገንዝበን፤» ብሎ ወደ እግዚአብሔር ለመነ። እግዚአብሔርም የማኑሄን
ቃል ሰማ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ በእርሻ ውስጥ ሳለች እንደገና ወደ
ሴቲቱ መጣ፥ እርሷም ፈጥና ባሏን ጠራችው፥ «እነሆ፥ አስቀድሞ ወደ እኔ
የመጣው ያ ሰው ደግሞ ተገለጠልኝ፤» ብላ ነገረችው። እርሱም፦
«ከሚስቴ ጋር የተነጋገርህ አንተ ነህን?» ብሎ ቢጠይቀው «እኔ ነኝ፤»
ሲል
መለሰለት። ማኑሄም፦ «እነሆ ቃልህ በደረሰ ጊዜ የልጁ ነገር፥ ግብሩስ
ምንድነው?» ብሎ ዳግመኛ ጠየቀ። መልአኩም ለሴቲቱ ነግሯት
የነበረውን
ሁሉ መልሶ ነገረው። ማኑሄ ለመልአኩ የፍየል ጠቦት ለማዘጋጀት
ቢፈልግም፦ «አንተ የግድ ብትለኝ እህልህን አልበላም፥ የሚቃጠለውንም
መሥዋዕት ብታደርግ ለእግዚአብሔር አቅርብ፤» አለው። ምክንያቱም
ቅዱሳን መላእክት ቅድሚያ የሚሰጡት ለእግዚአብሔር ክብር ነው።
እነርሱን ግን እግዚአብሔር ራሱ እንደሚያከብራቸውእንደሚያስከብራቸውም
ያውቃሉ።
ማኑሄ የተገለጠላቸው የእግዚአብሔር መልአክ እንደሆነ አላወቀም፥
ሚስቱም አላወቀችም። በመሆኑም፦ «ነገርህ በደረሰ ጊዜ እንድናከብርህ
ስምህ ማን ነው?» በማለት ጠየቀው።
የእግዚአብሔርም መልአክ፥ «ስሜ ድንቅ ነው፥ ለምን ትጠይቃለህ?»
ብሎታል። ማኑሄም የፍየሉን ጠቦትና የእህሉን ቊርባን በድንጋይ ላይ
ለእግዚአብሔር አቀረበ። መልአኩም ተአምራት አደረገ፥ ማኑሄና ሚስቱም
ይመለከቱ ነበር። ነበልባሉም ከመሠዊያው ላይ ወደ ሰማይ በወጣ ጊዜ
የእግዚአብሔር መልአክ በመሠዊያው ነበልባል ውስጥ ወደ ሰማይ ዐረገ፥
ማኑሄና ሚስቱም ተመለከቱ፥ በምድርም በግንባራቸው ወደቁ።
(ሰገዱለት)። ይህ መልካም የምሥራችን የተናገረ፥ የተለያዩ ተአምራትን
ያደረገ፥ መሥዋዕታቸውንም ወደ ሰማይ ያሳረገ፥ የእግዚአብሔር መልአክ
ቅዱስ ሚካኤል ነው። ሚካኤል ማለት በሁለተኛ ትርጉሙ «የእግዚአብሔር
ነገሩ ዕፁብ ድንቅ ነው፤» ማለት ነውና። መሳ ፲፫፥፩-፳። በዚህም የስሙ
ትርጓሜ ነገረ እግዚአብሔር መሆኑን እንረዳለን።
፩፥፪፦ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ፤ ኢያ ፭፥፲፬
ከነቢያት አለቃ ከሙሴ በኋላ በእርሱ እግር ተተክቶ የእግዚአብሔርን ሕዝብ
የመራው ኢያሱ ነው። የመረጠውም ሰው ሳይሆን እግዚአብሔር ነው።
እግዚአብሔርም፦ «በሕይወትህ ዘመን ሁሉ የሚቋቋምህ የለም፤ ከሙሴ
ጋር እንደነበርሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ አልጥልህም፥ ቸልም
አልልህም፤» ብሎታል። ኢያ ፩፥፭። ይህ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር የሆነለት
ታላቅ ሰው ኢያሱ የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት አስፈልጐታል።
ምክንያቱም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ለመሆኑ ምልክቱ ቅዱሳን መላእክት
ናቸውና። እግዚአብሔር ባለበት ቅዱሳን መላእክት አሉ፥ ቅዱሳን
መላእክትም ባሉበት እግዚአብሔር አለ። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደባት ሌሊት የምሥራቹን «እነሆ፥ ለእናንተና
ለሕዝቡ ሁሉ ደሰታ የሚሆን ታላቅ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤
እነሆ፥ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት ተወልዶላችኋል፤ ይኸውም ቡሩክ ጌታ
ክርስቶስ ነው።» በማለት ለእረኞች የነገሯቸው ቅዱሳን መላእክት ናቸው።
እረኞቹም፦ «እስከ ቤተልሔም እንሂድ፥ እግዚአብሔርም የገለጠልንን
ይህን
ነገር እንወቅ፥ አሉ።» ሉቃ ፪፥፮-፲፭። በዚህም ቅዱሳን መላእክት
የገለጡላቸውን ምሥጢር እግዚአብሔር ገለጠልን ብለዋል።
ኢያሱ ወልደ ነዌ፥ ሕዝቡን እየመራ በኢያሪኮ አጠገብ ሳለ ዐይኑን አንሥቶ
ቢመለከት እነሆም የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ የያዘ ሰው በፊቱ ቆሞ አየ። ወደ
እርሱም ቀርቦ «ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻ
ችን ወገን ነህን?» አለው።
እርሱም «እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ነኝ፤ አሁንም ወደ አንተ
መጥቻለሁ፤» ብሎታል። ኢያ ፭፥፲፫-፲፭። የእግዚአብሔር ሠራዊት
የሚባሉት
ቅዱሳን መላእክት ናቸው። «ያዕቆብም መንገዱን ሄደ፥ በዓይኖቹም
የእግዚአብሔርን ሠራዊት ከትመው አየ፥ የእግዚአብሔር መላእክትም
ተገናኙት። ያዕቆብም ባያቸው ጊዜ እነዚህ የእግዚአብሔር ሠራዊት ናቸው
አለ፤» ይላል። ዘፍ ፴፪፥፩-፪። ቅዱስ ዳዊትም፦ «ሠራዊቱ ሁሉ፥ ፈቃዱን
የሚያደርጉ አገልጋዮቹ፥ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤» ብሏል። መዝ
፩፻፪፥፳፩። የእነዚህም (የእግዚአብሔር ሠራዊት) አለቃቸው ቅዱስ ሚካኤል
ነው። ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ይሁዳ «የመላእክት አለቃ ሚካኤል»
በማለት መስክሮለታል። ይሁዳ ፩፥፲፪።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር !
Commenti